Thursday, March 13, 2014

የሚሊየኖች ድምጽ – የሚሊየኖች ድምጽ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በዉጭ ግብረ ኃይል ተቋቋመ !

አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ ከማንም የበለጠ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይረዳዋል ብለን እናምናለን። የኢሕአዴግ መንግስት፣ ላያ ላዩን «በዴሞክራሲ አምናለሁ» ቢልም፣ ፍጹም አምባገነን በሆነ መልኩ ፣ ሕዝቡን አፍኖ፣ እያሰራ፣ እየገደለ፣ ዜጎችን እያፈናቀለ፣ ከሃያ አመታት በላይ ቆይቷል። በአብዛኛዉ ሕዝብ ዘንድ እየተጠላ፣ ይሄን ያህል አመት በስልጣን መቆየት የቻለው፣ አገዛዙ በዋናነት ኢትዮጵያዊያን መከፋፈል በመቻሉና ዜጎች ደፍረው ለመብታቸው እንዳይቆሙ በፍርሃት እንዲተበተቡ በማድረጉ ነው። ይሄንን ለማስቆም ሕዝቡን ማስተባበርና ማደራጀት ቀዳሚና ብቸኛ አማራጭ ነው።
አገር ቤት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶ አሉ። ከነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ የአንድነት ፓርቲ ነው። የአንድነት ፓርቲ «የሚሊዮኖች ድምጽ ለፍትህ» እና «የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት» በሚል ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ይህ እንቅስቃሴ የአንድ ፓርቲ እንቅሳቅሴ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ፣ በአገራችን ዴሞክራሲና የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ሊቀላቀሉት፣ ሊደግፉት፣ የራሳቸው ሊያደርጉት የሚገባ እንቅስቃሴ ነዉ። ይህ እንቅስቃሴ የሚሊዮኖች እንቅስቃሴ ነው። የእያንዳንዳችን እንቅስቃሴ ነው።
በቅርቡ በባህር ዳር አስደናቂ ሰልፍ መደረጉ ይታወሳል። በቦታዉ የተገኙ ወገኖች ድምጻቸውን ያሰሙት አንድን ፓርቲ ብለው አልነበረም። ኢትዮጵያን ብለው ነዉ እንጂ። የባህር ዳሩ ሰልፉ ያማከለው በአንድ ድርጅት ዙሪያ አልነበረም። ነገር ግን በኢትዮጵያ ዙሪያ እንጂ። ይህ በባህር ዳር የተደረገውን አይነት የነጻነት እንቅስቃሴ በተጧጧፈ መልኩ በመላው አገሪቷ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።
በአገሪቷ ሕገ መንግስት አንቀጽ 30 መሰረት፣ የዜጎች የመሰባሰብ ፣ በሰላም ትእይንተ ሕዝብ የማድረግ ሙሉ መብት የተረጋገጠ ነው። በመሆኑም ይህ የሚሊዮኖች ለነጻነት ንቅናቄ ሰላማዊና የአገሪቷ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የሚደረግ በማንም ዜጋ ወይንም ቡድን ላይ ያላነጣጠረ፣ የተወሰኑትን ጠቅሞ ሌላዉን የሚጎዳ ያልሆነ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በመደብ፣ በጾታ ልዩነት ሳያደርግ፣ ኢትዮጵያዉያንን በሙሉ ለፍትህና ለነጻነት ለማሰባሰብና ለማንቀሳቀስ ታሰቦ የታቀደ እንቅስቃሴ ነው።
በዳያስፖራ ያለው ማህበረሰብም የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል እንደመሆኑ፣ የድርሻዉን መወጣት ይጠበቅበታል። በመሆኑም ይሄን የሚሊዮኖች ድምጽ ወይንም በባህር ዳር የተደረገዉን አይነት እንቅስቃሴ በሌሎች ከተሞች እንዲደረግ ለመርዳትና ለማጠናከር፣ የዳያስፖራ የሚሊዮኖች ድምጽ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ይህ ግብረ ኃይል በዳያስፖራ ባሉ የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ማህበራት አነሳሽነትና በዉጭ ካሉ የአንድነት ፓርቲ ድጋፍ ማህበራት በተጨማሪ፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግልን በሚደገፉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራት ፣ ፓልቶክ ክፍሎችና ግለሰቦች ተባባሪነት፣ «እኛም የሚሊዮኖች አንዱ አካል ነን» እያሉ ቀናና የሚያኮራ ኢትዮጵያዊ ምላሽ እየሰጡ ያሉና ለመስጠትም የተዘጋጁ፣ በአለም ዙሪያ ሁሉ ያሉ ኢትዮጵያዉያንን ለነጻነትና ለፍትህ ለማሰባሰብ የተዋቀረ ነው።
የሚሊየነሞች ንቅናቄ አዲስ አበባ እና ድረደዋ አስተዳደሮችን ጨምሮ፣ በኦሮሚያ የአዳማ፣ የላፍቶና የነቀምቴ ከተሞችን፣ በደቡብ ክልል፣ የአዋሳ፣ የጂንካና የቁጫ ወረዳዎችን፣ በትግራይ ክልል የመቀሌ ከተማን፣ በአማራዉ ክልል ደሴ፣ የወልዲያ፣ ደብረ ታቦር ፣ ደብረ ማርቆስ እና በምእራብ አርማጭሆ የአብርሃ ጅራ ከተማን ፣ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ የአሶሳን ከተማ፣ በጋምቤላ ክልል የ ጋምቤላ ከተማ የሚያዳርስ ይሆናል።
የሚሊየምን እንቅስቃሴን በተመለከተ በየጊዜዉ ወቅታዊ መግለጫ የምንሰጥ መሆናችንን እየገለጽን። በዉጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ እንደከዚህ በፊቱም ታላቅ ድጋፉን እንዲያበረክት በአክብሮት እንጠይቃለን። አገራችን ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ አገር ናት። ለአገራችን መነሳታችን ሊያስከፋ የሚችለው፣ ወይንም ዝምታን ተስፋ ቆርጠን መቀመጣችን ሊያስደስት የሚችለው አምባገነኖችን ብቻ ነው። በሕዝባችን ላይ ግፍ የሚፈጽሙ አይደሰቱ። እንነሳ። የድርሻችንን እንወጣ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !
በምትኖሩበት ከተማ ተደራጅታችሁ፣ ከዚህ ግብረ ኃይላ ጋር በመስራት በአገር ቤት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ስፖንሰር ማድረግ የምትፈልጉ በሚከተሉት አድራሹ ሊያገኙን ይችላሉ
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
millionsforethiopia@gmail.com
404- 518-7858
ምንጭ፣ http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/13502

No comments:

Post a Comment