Wednesday, February 1, 2017

በአርበኞች ግንቦት 7 ስም የተከሰሱት እነ ንግስት ይርጋ በቀረበባቸው ክስ ላይ ያለቸውን ተቃውሞ አቀረቡ | መቃወሚያውን ይዘነዋል

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት የተዘጋጀ
(ጥር 23/2009) አርበኞች ግንቦት ሰባት ከተባለ ሽብርተኛ ቡድን ተልእኮ በመቀበል እና የሽብር ቡድኑ አባል በመሆን በአማራ ክልል ውስጥ ከ2008 መጨረሻ እስከ 2009 መጀመሪያ ከ200 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ የሚል ክስ የቀረበባቸው እነ ንግስት ይርጋ ( ስድስት ሰዎች)፤ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32[1] (ሀ) እና (ለ)፣ አንቀፅ 38 እና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3 (4) እና (6) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ተብሎ ከአራት ወር የማእከላዊ ቆይታ በኋላ ከሶስት ሳምንት በፊት ክስ እንደተመሰረተባቸው የሚታወስ ነው።
በዛሬው ችሎት የሁሉም ተከሳሽ ጠበቆች በክሱ ላይ ያላቸውን መቃወሚያ ለችሎት በፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ ለአቃቤ ህግም የመቃወሚያው ቅጂ እንዲደርሰው ተደርጓል።
6ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ያሬድ ግርማ ከ500 ገፅ በላይ የሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ፊደል ላይ ያደረገው ጥናት ከማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ማእከል እንዳልተመለሰለት ገልፆ፤ ከማእከላዊ ሲወጣ ወደ ማረሚያ ቤት እንደሚላክለት መርማሪዎች ነግረውት እንደነበር አስታውሶ እስካሁን ግን እንዳልተላከለት በመናገር እንዲሰጠው ትእዛዝ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

5ኛ ተከሳሽ የሆነው በላይነህ አለምነህ፤ ፀረ ሽብር ህጉ በህገመንግስቱ አንቀፅ 20(መ) የተቀመጠውን “ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማንኛውም ማስረጃ የመመልከት” እንዲሁም በህገመንግስቱ አንቀፅ 26(ለ) የተቀመጠውን “በስልክ እና በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚደረጉ ግንኙነቶች አይደፈሩም” የሚለውን ድንጋጌ በመሻር እና ባጠቃላይ ህገ መንግስቱ ተጥሶ የወጣ አዋጅ እንደሆነ ተናግሮ ይህን ህገ መንግስት ለመጠበቅ በየተዋረድ ያሉ የመንግስት አካላት ሃላፊት ያለባቸው መሆኑን ተናግሯል። ዳኞችም ምን አይነት ማስረጃ እንዳልደረሰው 5ኛ ተከሳሽ በላይነህን ጠይቀውት የሰው ምስክር ማስረጃን በተመለከተ ምንም የደረሳቸው ማስረጃ እንደሌለ መልሷል። ዳኞችም የምስክሮችን ደህንነት መጠበቂያ እራሱን የቻለ መመሪያ እንዳለ ተናግረው፤ በሱ መሰረት ለምስክሮች ደህንነት ሲባል አድራሻቸውን እና ስማቸውን ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር አለመያያዙ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቃቤ ህግ ተከሳሾች ባቀረቡት ተቃውሞ ላይ ያለውን አስተያየት ለመቀበል ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 7/2009 ተሰጥቷል።
በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ ንግስት ይርጋ ተፈራ ( እድሜ 24, ሰሜን ጎንደር)
2ኛ አለምነህ ዋሴ ገ/ማርያም ( እድሜ 57, ሰሜን ጎንደር)
3ኛ ቴዎድሮስ ተላይ ቆሜ ( እድሜ 18, ሰሜን ጎንደር)
4ኛ አወቀ አባተ ገበየሁ ( እድሜ 31, አዲስ አበባ)
5ኛ በላይነህ አለምነህ አበጀ ( እድሜ 29, ባህር ዳር)
6ኛ ያሬድ ግርማ ሃይሌ ( እድሜ 46, አዲስ አበባ)
የክስ መቃወሚያዎቹን ዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ሊንኮች ይጫኑ
ምንጭ : http://www.zehabesha.com/amharic/archives/71841