Monday, February 10, 2014

Health: የጨጓራ ህመሜ ወደ ካንሰርነት ተቀይሮ ይሆን? መፍትሄውን ጠቁሙኝ እባካችሁ

ዕድሜዬ 43፣ ፆታዬ ወንድ፣ ስራዬ ደግሞ በግል ስራ የምትዳደር፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የተጠናወተኝ ጨጓራ እስካሁን ያሰቃየኛል፡፡ አንቲ አሲድ ሽሮፕና የጨጓራ ክኒኖች ቀለቦቼ ናቸው፡፡ በሳምንት ውስጥ ውስጤ ሳይቃጠል በሰላም የማሳልፋቸው ቀናት ሁለት አይሞሉም፡፡ የጭንቀቴ መንስኤ ግን ይህ የጨጓራ ህመም ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ እንደ እኔው በኃይለኛ ጨጓራ ሲቸገር የነበረው አባቴም በመጨረሻ ችግሩ የጨጓራ ካንሰር ሆኖ ተገኘ፡፡ ሐኪሞቹም በኦፕሬሽን ሊሞከር ከሚቻለው በላይ ተስፋፍቷልና ጨረር ይሞከርለት ተብሎ ነበር፡፡ እሱም ብዙም ሳይረዳው ካረፈ ዓመት ሞላው፡፡ እናም እኔም ጨጓራዬ በለበለበኝ፣ ቃር በበዛብን ቁጥር ውስጤን ከሚሰማኝ የማቃጠል ፀባይ ይበልጥ የሚረብሸኝ ወደ ካንሰርነት ተቀይሮ ይሆን? ወይ የሚለው ስጋቴ ነው፡፡ ይሄን ስጋቴን በምን ላጥፋው? ወደ ካንሰርነት ተቀይሮ ከሆነስ የኦፕሬሽ ጥቅም እምን ድረስ ነው?
ተድላ ነኝ

ask your doctorየዶ/ር ዓብይ ምላሽ፦ ውድ ተድላ ጥያቄህን ከአክብሮት ጋር በሚከተለው መንገድ አስተናግደነዋል፡፡ በተለምዶ ጨጓራ እያልን የምንጠራው ህመም ለጨጓራ ብቻ የተወሰነ ህመም ሳይሆን ትንሹን አንጀት ጨምሮ በተናጠል ወይንም በጋራ የውስጥ ግድግዳቸው ተልጦ ሲቆስል የሚኖር የማቃጠል የህመም ስሜት ነው፡፡ ቃር፣ ደረት እና ከእምብርት በላይ ማቃጠል፣ ጀርባ እና ውስጥ እጅ መንደድ፣ ማግሳት፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ሁሉ ከጨጓራ ህመም ምልክቶች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ የጨጓራ ካንሰርም ተመሳሳይ ምልክቶች ሊኖሩት ሲችሉ ጨጓራ ካንሰር ቁስሉ የሚገኘው ግን እዛው ጨጓራ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የካንሰርነት ባህሪይ ያላቸው ሴሎች ግን ከጨጓራም አልፈው አካባቢውን ሊያዳርሱት ወይንም በደም እና ሊምፍ አማካኝነት ወደ ሩቅ ቦታ ሊዛመቱ ይችላሉ፡፡
ውድ ዓለሙ አባትህን በጨጓራ ካንሰር ማጣትህ ጭንቀትህን ቢያንረው አያስገርምም፡፡ አስፈላጊውን ምርመራዎች በማድረግ ግን ይህን ጭንቀትህን ማስወገድ ትችል እንደነበር ስንነግርህ አሁንም አልረፈደምና ምርመራዎችን ልታደርጋቸው እንደምትችል ልናሳስብህ እንወዳለን፡፡
በመጀመሪያ የጨጓራ ካንሰር ጠቋሚ ምልክቶችን ለማብራራት ያህል የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፡፡ የጨጓራ ካንሰር ዕድሜ ሲገፋ ይበልጥ የሚስተዋል ህመም እንደመሆኑ
ከአርባ ዓመት ዕድሜ በኋላ ድንገት የሚጀምር የጨጓራ ህመምን በቸልታ ማለፍ አያስፈልግም፡፡ አዲስ የተነሳ የጨጓራ ህመም ብቻም ሳይሆን ድንገት ከአርባዎቹ ዕድሜ በኋላ ተባብሶ እረፍት የሚነሳ የጨጓራ ህመምንም ሐኪም ጋር ቀርቦ የጨጓራ ካንሰር አለመሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡
ክብደት መቀነስ፣ ሆድ ላይ የሚስተዋል እብጠት ወይንም ምግብ መዋጥ አለመቻልም እንዲሁ ከጨጓራ ህመም ምልክቶች ጋር በህብረት ከታዩ የጨጓራ ካንሰር ተከስቶ ሊሆን ይችላልና መዘግየት አያስፈልግም፡፡
ask your doctorከሁሉ ይበልጥ ግን የጨጓራ ክኒኖችን እየዋጥክ የማቃጠል ስሜቱን ለማሸነፍ ከመጣር ይልቅ በደንብ ልትመረመር እና ልትታከም ይገባል፡፡ በቀላሉ አልታገስ ያለ የጨጓራ ህመም ሔሊኮባክተር ፓይሎሪ በሚባለው ባክቴሪያ አማካኝነት የተነሳ የጨጓራ ህመም ሊሆን ይችላልና በቀላል የደም ምርመራ ማወቅ ይቻላል፡፡ ህክምናውም እጅግ ቀላል ሲሆን ሶስት አይነት መድሃኒቶችን (ሁለት አይነት አንቲ ባዮቲክስ እና አንድ የአሲድ ምርት የሚቀንስ ታብሌት) ለሁለት ሳምንት ብቻ በመውሰድ ለዓመታት የጨጓራ ህመም እንዳይመለስ ያደርጋል፡፡
ባክቴሪያው በደም ምርመራ እንደሌለ ከተረጋገጠና ሐኪምህ የጨጓራህን ቁስል ባህሪይ ለማወቅ ከፈለገ (የካንሰርነት ባህሪይ ይኑረው፣ አይኑረው) የራጅ ምርመራ ያደርግልሃል፡፡
ይሄኛው የራጅ ምርመራ ግን ከተለመደው የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የጨጓራህን ውስጣዊ ግድግዳ ያለበትን ሁኔታ በራጁ እንዲታይ አስቀድመህ የምትጠጣው ኬሚካል ይኖራል፡፡ ወይንም ደግሞ ሐኪምህ በኢንዶስኮፒ የጨጓራህን ውስጣዊ ግድግዳ ሊመለከትና ከተጠራጠረም ከቁስሉ አካባ ናሙናዎችን ወስዶ በፓቶሎጂ ምርመራ የካንሰርነት ባህሪይ እንዳለውና እንደሌለው ማረጋገጥ ይችላል፡፡
ገና በ43 ዓመት ዕድሜህ ህመምህ የጨጓራ ካንሰር የመሆን ዕድሉ እጅግ አናሳ ቢሆንም ጥያቄህን ለመመለስ ያህል ለጨጓራ ካንሰር የሚደረገው ህክምና በዋነኝነት በኦፕሬሽን ቆርጦ ማውጣት መሆኑን ልንጠቁምህ እንወዳለን፡፡ በሽታው ሳይሰራጭ ከተደረሰበት ከካንሰሩ ሙሉ ለሙሉ የመፈወስ እድል ሲኖር ብዙው ጊዜ ግን ይህ አያጋጥምህም፡፡ በተጨማሪም ከቦታው አልፎ ለተስፋፋ የጨጓራ ካንሰር ከኦፕሬሽ ጎን ለጎን የጨረር ህክምና መስጠትም ይቻላል እያልን ወድ ተድላ ሳትዘገይ ሐኪም ዘንድ ቀርበህ ትታይ ዘንድ በድጋሚ እንመክርሃለን፡፡
ምንጭ፣ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12669

No comments:

Post a Comment