Sunday, February 9, 2014

የቤተ መንግስት ዙሪያ መፈክሮች!

 

ከቤታቸው ሽፈራው
ድሮ በቤተ መንግስት ዙሪያ ሳልፍ የሆነ ነገር ይጫጫነኝ ነበር፡፡ በቃ! ቤተ መንግስቱ አንዳች ጣኦት የሚመለክበት፣ አሊያም ባዕድ ነገር የሞላው አድርጌ ስለምቆጥረው በአካባቢው ማለፍ ይከብደኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ቤተ መንግስቱ አጥር ላይ የተሰቀሉት ጽሁፎች ይህን ድባብ በትንሹም ቢሆን ቀይረውልኛል፡፡ እነዚህ መፈክሮች ሁሌም ያስፈግጉኛል!
meles fun
የአቶ መለስ ሞት ከተነገረ በኋላ እንደ ማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ ቤተ መንግስት የመግባት እድል ባገኝም ለመግባት ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ አንድ ቀን እንደምንም ደፍሬ በለቅሶ ስም ይህን የምጠላውን ቤተ መንግስት ለመጎብኘት ወንድሜን ሳማክረው ‹‹መለስን ያልሰራውን ሰራ እያሉ የሚዘሉ የሚፈርጡትን ካድሬዎች ስናይ ሳቃችን ያመልጠናል፡፡ ይቅርብን!›› የሚል ጠቃሚ ምክር ስለለገሰኝ ቤተ መንግስቱን ሳላየው ቀርቻለሁ፡፡
በእርግጥ ቤተ መንግስት ውስጥ ለማስመሰል ሲዘሉ የነበሩትን ካድሬዎች በኢቲቪ መስኮትም አይቼ ሆዴን ጨብጩ ስቄያለሁ፡፡ የፈረንሳይ ልጆች ደግሞ ይህን የካድሬዎች የለበጣ ለቅሶ ‹‹አሸባሪ በለኝ፣ አንድ ለአምስት ጠርንፈኝ፣ የምርጫ ኮረጆ ልገልብጥልህ፣ ትምክተኝ ብለህ ስደበኝ፣ ተንበርካኪ በለኝ፣ ልማታዊ በለኝ፣ በይቅርታ አስፈርመኝ፣…….›› እያሉ በሽሙጥ ሲያለቅሱ እንደልባችን እየሳቅን የምንታደምበትን ቤተ መንግስት (ፈረንሳይ) መረጥን!
ቤተ መንግስት ባንገባም ስለ አቶ መለስ የሚባሉትን ነገሮች ከአልቃሾቹ እኩል በኢቲቪና ጎዳና ላይ እንከታተላለን፣ እናነባለን፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ መንግስቱ ዙሪያ የተሰቀሉት መፈክሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ሰሞን ላይ እነዚህን ጽሁፎች ስመለከት በሚቀፈኝ መንገድ እንደ እብድ ገጥጨበታለሁ፡፡ በርካቶችም ልክ እንደ እኔ ሲስቁ ተመልክቻለሁ፡፡
ከአራት ኪሎ በኩል በሚገኘው የቤተ መንግስቱ ጫፍ ላይ ‹‹ጀግና አይሞትም!›› የሚል መፈክር ከአቶ መለስ ፎቶ ጋር ተሰቅሏል፡፡ ይህኔ ከአርጀንቲና ቮልቪያ፣ ከዛም ኩባ፣ ከደቡብ አሜሪካ ወደ አፍሪካዋ ኮንጎ በጎሳ፣ ዘውግ፣ ሀይማኖት፣ ቀለም የማይመሳሰሉትን ዜጎች ከጭቆና ለማውጣት የባዘነውን ‹‹ቼ››ን አሰብኩት፡፡ ሁችሚኒ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ቴዎድሮስ፣ በላይ፣ አቢቹ፣ አሉላ፣ አብዲሳ አጋ…….ህዝብን በጎሳና ዘውግ ሳይከፋፍሉ መሞታቸውን አስታወስኩ! ታዲያ የትኛው ጀግና ነው የማይሞተው? ነው የጀግና ትርጉም ተቀየረ? እያልኩ በማሰላሰል ላይ እያለሁ ሁለተኛውን መፈክር ተመለከትኩ፡፡
‹‹ዓለም ያጣችው ምርጥ መሪ!›› የሚል ነው፡፡ ዓለም ቤተ መንግሰቱ ነው? አዜብ መስፍን ናቸው? ቻይና ነች? እያልኩ ከራሴ ጋር ስቀልድ የመጀመሪያውን መፈክር በሙሉ ድምጽ የሻረ ሌላ መፈክር ተሰቅሎ አየሁ፡፡ ይህኛው ጉደኛ መፈክር ‹‹የጀግና እረፍቱ ሞቱ ነው!›› ይላል፡፡
ይህ ለሌላ ሰው ነው እንዳልል የአቶ መለስ ፎቶ ተለጥፎበታል፡፡ አዎ! ለመጀመሪያ ጊዜ ያንን በዓድ መንገድ ረዥም ሳቅ ሳቅኩበት፡፡ በቤተ መንግስቱ አስቂኝ መፈክሮች መሰረት 20ና 30 ሜትር ውስጥ ዘላለማዊ የነበረ ‹‹ጀግና›› ለእርፍት ወደ ሰማይ ቤት ያመራል፡፡ በዛን ሰሞን ወይዘሮ አዜብ መስፍን ቤተ መንግስቱን የራሳቸው ንብረት አድርገው ‹‹እዩት የእኛን ቤት፣ ይህ ነው የእኛ ቤት፣….›› እያሉ ሲያስጎበኙ በጣት የሚቆጠሩ ሰከን ያሉ ካድሬዎች ሳይቀሩ ‹‹እኒህ ሴትዮ ጭራሹን ባሰባቸው›› ብለው አሽሟጥጠዋል፡፡ እኔም ምን አልባት እነዚህ ጽሁፎች በአዜብ መስፍን ትዕዛዝ የተሰቀሉ ቢሆኑስ? የሚል ሀሳብ መጣብኝ፡፡ ደግሞ ‹‹ቤቴ ነው!›› ከሚሉት ቤተ መንግስት አጥር ድረስ ይቅርና ሳውዲና ስይዘርላንድ ድረስም በአገሪቱ ገንዘብ የሚያንጋጉዋቸው ታማኞች እንዳሏቸው አውቃለሁ፡፡ ከወይዘሮ አዜብ ጋር ቤተ መንግስቱ ውስጥ ሲያለቅሱ የነበሩትን ግራ አጋቢ ካድሬዎች አስታወስኩ! ግራ የተጋቡ ካድሬዎች በበዙበት መፈክሮቹም የትየለሌ ናቸው!
አንዳንዶቹ ከጎኑ ደግሞ ምን አልባትም አቶ መለስ አምስትና ስድስት አመታቸው የተነሱት ፎቶ ግራፍ አብሮ ተለጥፏል፡፡ አቶ መለስ በአምስትና ስድስት አመታቸው ጀምረው ነው ኢትዮጵያን ሲመሩ የኖሩት ከሚል እሳቤ የመጣ መሆን አለበት፡፡ ይህኛው ደግሞ ከሀይማኖት አባትነታቸው ይልቅ ካድሬነታቸው ከሚያመዝነው ‹‹የሀይማኖት አባቶች›› የተበረከተ ይሆናል፡፡ ልክ እየሱስ ክርስቶስ ልጅ ሆኖም ጌታ እንደነበረው ማለት ነው፡፡
አሁን የቤተ መንግስቱን አጥር እያጋመስን ነው፡፡ ሌላ መፈክር! ‹‹አንተ ብትሞትም ራዕይህ ይቀጥላል!››፡፡ ይህኛው እረፍትም ሆነ ዘላለማዊነት የለውም፡፡ በእነዚህ መፈክሮች ተቃርኖ ሳቄን ሳላባራ ማዶ ላይ በላቸው ግርማ ከአንዲት አሮጊት፣ ሸገር ብሎ ደግሞ ከወት ጋር ተንጋሎ እየሳቀ ተመለከትኩት፡፡ እነዚህ መፈክሮች አይደለም አንተን? ሌላ ቀን ግርማቸው በደረቁ ነው የሚስቀው፤ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ያለው ግርማቸው ግን ሁሌም ከምር ይንፈረፈራል! እኔም ተክዤ፣ ተናድጄ፣ ደክሞኝ ውዬም ቢሆን የምስቀው ቤተ መንግስት ስደርስ ነው፡፡
የገረመኝ የኃይሌ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ በሚስቁበት ጎዳና ሁሌም አረቄውን ከፊቴ አጋድሞ ይሮጣል፡፡ ከፊቱ ላብም ይሁን እንባ ብቻ የሆነ ነገር ይታየኛል፡፡ እምባ መሆን አለበት፡፡ የመፈክሮቹን ተቃርኖ የተመለከተማ (በአረቄ) ስካር የተጻፉ ስለነሆናቸው ቢጠረጥር አይፈረድበትም፡፡ መጠርጠር ነው!
ምንጭ፣ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12647

No comments:

Post a Comment