Wednesday, February 26, 2014

Health: ነብሰ ጡር ሴቶች ሊወስዷቸው የሚገቡ 5 ክትባቶች


ይህ ትምህርታዊ ዘገባ የቀረበላችሁ በሚኒሶታ የጤና ዲፓርትመንት (MDH)፤ ከዘ-ሐበሻ ጋር በመተባበር ነው።
1. አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ለመጀመሪያ ጊዜ የቅድመ ወሊድ ክትትል ሐኪም ዘንድ ታይታ መመለሷ ነው። ሐኪሙም ራሷን እና በማደግ ላይ ያለውን ፅንስ ጤንነት በምን መልኩ መጠበቅ እንደምትችል ሰፊ መረጃ ያለው እሽግ ሰጥቷታል። ከማድረግ ልትቆጠባቸው የሚገቡ በርካታ ዝርዝር ነገሮችን አካቷል፤ አንዳንድ የምግብ አይነቶችን እንዳትመገብ እና አንዳንድ መጠጦችን ደግሞ እንዳትጠጣ ገደብ አድርገዋል፤ እንዳታጨስ፣ የድመት መጸዳጃ ስፍራን እንዳታጸዳ እና ሌሎችም በርካታ ነገሮች ከማድረግ እንድትቆጠብ ነግረዋታል። እርሷም ግራ ተጋብታለች ምክንያቱም ከማድረግ እንድትቆጠብ የተነገሯት ነገሮች እጅግ ብዙ ሲሆኑ፣ ዓላማውም ራሷን ከተጋላጭነት እንድትጠብቅ ወይም ወደ ሰውነቷ ውስጥ የገባ ነገር በፅንሱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ነው፤ በሌላ በኩል ሐኪሟ የጉንፋን እና የሳል/የትክትክ ክትባት እንድትከተብ ምክር ሰጥተዋታል። በልጇ ላይ ጉዳትን የሚያስከትል ማናቸውም ነገር ማድረግ ስለማትፈልግ በእርግዝና ወቅት መከተብ በፅንሱ ላይ ጉዳት ያደርስ ይሆን የሚል ጥያቄ ጭሮባታል።
MDH Amharic
2. በእርግዝና ወቅት ነፍሰ ጡር ሴቶች እንዲወስዷቸው የሚመከሩ ክትባቶች በነፍሰ ጡሮች እና በፅንስ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት የለም፤ ይልቁንም ለጤናማ እርግዝና ከፍተኛ አስተዋጽዖ አላቸው። የሚኒሶታ የጤና መምሪያ (MDH) ነፍሰ ጡር ሴቶች በእያንዳንዱ የእርግዝና ወቅት ሁለት ክትባቶች እንዲወስዱ ይመክራል፡- የኢንፍሉዌንዛ ክትባት (በተለምዶ የጉንፋን ክትባት በመባል የሚታወቅ) እና ፔርቱሲስ ወይም የሳል/የትክትክ ክትባት (ይህም የቴታነስ፣ የዲፍቴሪያ እና ፔርቱሲስ (Tdap) ያካተተ ነው)። የነፍሰጡሯ ሐኪም ከላይ ከተገለጹትም በተጨማሪ ሌሎች ክትባቶች ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ጊዜ እና ከእርግዝና በኋላ እንዲወሰዱ ምክር ሊሰጡ ይችላሉ፤ በዚህም ወቅት የነፍሰጡሯ ዕድሜ፣ ሌሎች የጤና ሁኔታዎች፣ ወደ ውጭ ሃገር ለመጓዝ የተያዘ ዕቅድ መኖሩ ወይም ቀደም ሲል የተወሰዱ ክትባቶች ያሉ መሆኑን ከግምት ውስጥ ይገባሉ።
3. ክትባቶች የነፍሰ ጡር ሴቶችን እና የአራስ ልጆቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳሉ። አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከተከተበች በኋላ ከክትባቱ ያገኘችውን በሽታ የመከላከል ብቃት ለፅንሱ ታስተላልፋለች። ይህም ሁኔታ አራስ ልጇ ክትባት እስኪያገኝ/እስክታገኝ ድረስ ከልደት በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከአንዳንድ በሽታዎች እንዲጠበቅ/እንድትጠበቅ ያደርጋል። ከዚህም ሌላ ክትባቶች ለነፍሰ ጡር ሴቶች እና ለሕጻናት ልጆቻቸው አደገኛ ሊሆኑ በሚችሉ አንዳንድ በሽታዎች እንዳይያዙ ይጠብቋቸዋል።
4. ነፍሰ ጡር ሴቶች የኢንፍሉዌንዛ (የጉንፋን) ክትባት መከተብ አለባቸው፤ ምክንያቱም በጉንፋን ምክንያት በጽኑ ሊታመሙ ይችላሉ። በእርግዝና ወቅት የጉንፋን ክትባት የሚከተቡ ሴቶች ጊዜውን ባልጠበቀ ምጥ የመያዝ ዕድላቸው እጅግ አናሳ ይሆናል፤ ፅንሱም ሕይወቱን የሚያጣበት ወይም ዝቅተኛ ክብደት ኖሮት የሚወለድበት ዕድል እጅግ አነስተኛ ይሆናል፤ ከወሊድም በኋላ በሆስፒታል ተኝቶ መታከም አስፈላጊ የሚሆንበት ዕድል ዝቅተኛ ይሆናል። አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በእርግዝና ላይ ሳለች በማናቸውም ጊዜ የጉንፋን ክትባት ብትወስድ በጤናዋ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም፤ በፅንሱም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም።
5. ከዚህም ባሻገር ነፍሰ ጡር ሴቶች በእያንዳንዱ የእርግዝና ጊዜ የTdap ክትባት መውሰድ ይገባቸዋል፤ ይህ ክትባት በእርግዝናው ከ27ኛ እስከ 36ኛ ሳምንት ባለው ጊዜ (በሦስተኛው የእርግዝና ክፍለ ጊዜ) ቢሰጥ ተመራጭ ይሆናል። የTdap ክትባት ነፍሰጡሯን ሴት እና ልጇን ከሳል/ትክትክ ይጠብቃል። ይህ በሽታ የጨቅላ ሕጻናትን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፤ ሆኖም ግን በእርግዝና ወቅት እናቶች የTdap ክትባት ከተከተቡ ልጆቻቸው ሙሉ በሙሉ ክትባት እስኪያገኙ ድረስ እንዲህ ካለው የሳል/የትክትክ ሕመም እንዲጠበቁ ይረዳል። ነፍሰ ጡር ሴቶች ሊያደርጓቸው የማይገቡ በርካታ ነገሮች ያሉ ቢሆንም፣ አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት የራሷን እና የልጇን ጤና ለመጠበቅ ልታደርጋቸው የምትችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ነፍሰ ጡር ሴቶች ልጅ ለመውለድ በሚዘጋጁበት ጊዜ “መደረግ ያለባቸው” ከሚለው ዝርዝር ላይ መከተብ የሚለው መደረጉን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ነፍሰ ጡር ሴቶች ሊወስዷቸው ስለሚገቡ ክትባቶች መረጃ ለማግኘት የሚከተለውን ድረ-ገጽ ይጎብኙ፡- www.cdc.gov/vaccines/adults/rec-vac/pregnant.html
ምንጭ፣ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/13167

No comments:

Post a Comment