Thursday, February 13, 2014

መኢአድና አንድነት ፓርቲ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡

ከአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ !!!!
ብአዴን ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ የመምራት የሞራል ልዕልና የለውም፤ ህዝብ ያዋረዱ አመራሮቹም ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚገነዘበው በዚህች ታሪካዊት እና የጥቁር ህዝብ ድል ማዕከል፤ የነፃነት ተምሳሌትና የአፍሪካ ህዝብ ኩራት በሆነች ሀገር የኋላ ዘመን ውጣ ውረድ ውስጥ ሰፊው የአማራ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድ ተሰልፎ ለሀገር ግንባታ ተኪ የሌለው ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአምባገነኖች ጡጫ ተደቁሷል፡፡ ዛሬም እንደ ትላንቱ በገዢዎቹ እየተረገጠ ያለ ህዝብ ነው፡፡
ይህ ህዝብ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም በየጋራው እና በየሸንተረሩ ተበታትኖ የኔ እንዳይላት እንኳን በተነፈገው ኩርማን መሬት አፈር እየገፋ ለመኖር መዳረጉ ሳያንስ የኢህአዴግ ፖለቲካ ሌላ ሰቀቀን ጨምሮ ‹‹ጨቋኝ ገዥ መደብ የነበረ፤ ትምክህተኛ›› በሚል ጎራ መድቦ ያልዘራውን ግፍ እንዲያጭድ እያደረገው እንደሆነ ይስተዋላል፡፡
የአማራ ህዝብ እንደሌላው ጭቁን የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ዘመኑ ባነበራቸው የአገዛዝ ሥርዓቶች የጭቆና ቀንበር ተጭኖት፤ የግፍ ፅዋ የተጋተ መሆኑ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን ህዝብ እወክላለሁ የሚለው የትላንቱ ኢህዴን የዛሬው ብአዴን ያፈራቸው አመራሮች ስልጣን በመቆናጠጥ የገዛ ህዝባቸውን ከመናቅና ከማዋረድ አልፈው ‹‹ትላንት ሽርጣም ያለህ ትምክህተኛ አንገቱን ይድፋ ዛሬ ተራው ያንተነው›› በማለት በግፍ እንዲገደል ማድረጋቸው ሰቆቃው ከህዝብ ህሊና ሳይወጣ አቶ መለስ ‹‹ጫካ መንጣሪ ሞፈር ዘመት›› ብለው እንደተሳለቁበት ሁሉ በሳቸው ራዕይ አስቀጣይ በዛሬዎቹ የብአዴን አመራሮችም ያው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ አገዛዙ የደረሰበትን አሳፋሪ ደረጃ በግልፅ ያሳያል፡፡
የክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት እና የብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን በቅርቡ አደረጉት ተብሎ የተደመጠው አስነዋሪ ንግግርም የክልሉን ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የናቁ እና ያዋረደ፤ የሀገሪቷን ህገ- መንግስት በግልፅ የጣሰ የወንጀል ተግባር ነው፡፡ በተጨማሪም የአማራን ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ለመነጠልና አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር የተደረገ ዘመቻ ነው፡፡
የኢህአዴግ አገዛዝ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከተጫነበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ክልል ያለው ህዝብ በራሱ ቋንቋ ተናጋሪዎች በግፍ እየተገዛ፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተገፍፎ በድህነት አረንቋ ውስጥ እየኖረ ቢሆንም የአማራን ህዝብ እንወክላለን እንደሚሉት ብአዴኖች የሚመራውን ህዝብ በአደባባይ በተደጋጋሚ የዘለፈ፤ ያዋረደ እና አንገት ያስደፋ ድርጅት አለ ለማለት ይቸግራል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የአማራን ህዝብ የመምራት የሞራል ልዕልና የሌለውን ብአዴን ኢህአዴግን ለመታገል መላውን አባላትና ደጋፊዎቻችንን ከጎናችን በማሰለፍ በፅናት እና በብቃት መታገል ያለብን ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደሆንን እንገነዘባለን፡፡
መላውን ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አንቀሳቅሰን ሰላማዊ ትግሉን ፍሬያማ በማድረግ አገዛዙ እንዲለወጥ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ የጀመርነውን ሰላማዊ ትግል አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እያረጋገጥን የካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በስርዓቱ ላይ ያለንን ተቃውሞ እናሰማለን፡፡ ይህ ትግል ህዝብ ያዋረዱ አመራሮች በተገቢው ፍጥነት ለፍርድ እስኪቀርቡ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የባህርዳር እና አካባቢው ነዋሪዎችም በነቂስ በመውጣት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን እንዲገልፅ ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ድል የህዝብ ነው !!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!!
ምንጭ፣ http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/13175

No comments:

Post a Comment