Monday, December 9, 2013

Health: ፍሬዬ ቦታውን ለቆ ወደ ውስጥ እየገባ ተቸግሬያለሁ


ከቅርብ አመታት ጀምሮ የቆለጥ ፍሬዬ ቢያንስ ለ1 ሰዓት ቦታውን ለቆ ወደ ውስጥ ማለትም ወደ ንፍፊቴ ከገባ በኋላ ከዚያ ወደ ትክክለኛው ቦታ ሲመለስ ያብጥና እጅግ በጣም ያመኛል፡፡ ራሴንም እስከመሳት ያደርሰኛል፡፡ ከዚያ ከ1-3 ቀን በኋላ ወደ ህክምና ስሄድ የሚሰጡኝ መፍትሄ የአባላዘር መድሃኒት ቢሆንም በፊት በፊት እጠቀም ነበር፤ በኋላ ግን ይህ በሽታ የአባላዘር እንዳልሆነና እኔም በሽታው የጀመረኝ በራሱ እንጂ ምንም አይነት የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዳላደረኩኝ ስገልፅላቸው ሌላ መድሃኒት ይቀይሩልኛል፡፡ ይህ ምንም መፍትሄ አላመጣልኝም፡፡ በሽታው በስድስት ወር አንዳንዴም በዓመት እየተመላለሰብኝ አስቸግሮኛል፡፡ የሚድነውም በመድሃኒት ሳይሆን በአጋጣሚ ከብዙ ስቃይ በኋላ እየሆነ መጥቷል፡፡ አሁን አሁን በብልቴ ላይ የሚገኘው ደምስር ከነበረው እየወፈረ መጥቷል፡፡ ለጊዜው በሽታ ባይኖረውም ስጋት ፈጥሮብኛል፡፡ ይህንን ችግሬን ተረድታችሁ ምላሽ እንደምትሰጡኝ እተማመናለሁ፡፡ ዮናስ
ask your doctor
የዶ/ር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፡ ውድ ዮናስ እንደምን ከርመዋል? ለችግርዎ መፍትሄ እነሆ ብለናል፡፡ በብልት አካባቢ የተለያዩ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በዋናነት የአባላዘር በሽታዎች በብልት አካባቢ ችግር እንደሚፈጥሩ ቢታወቅም፣ ከአባላዘር በሽታ ውጪ የሆኑ የመራቢያ አካላትን ሊያበግኑ የሚችሉ በሽታዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ ከመራቢያ አካላት አፈጣጠር ጉድለት የተነሳ ችግሮች ሊከሰቱ ሲችሉ፣ በአግባቡ የተፈጠረ የመራቢያ አካልም በአደጋና በተለያዩ ምክንያቶች ሊቃወስ ይችላል፡፡
ውድ ዮናስ ፡- እርስዎ የአባላዘር በሽታ ህክምና ሊያድንዎት አለመቻሉ እንዲሁም፣ የቆለጥዎ ወደ ንፍፊት አካባቢ እየገባ መጥፋት የሚያሳየው አንዳች የአፈጣተር ጉድለት በብልትዎ አካባቢ መኖሩ ነው፡፡ በሰው አፈጣጠር ሂደት ውስጥ በሆድ ዕቃና በቆለጥ ከረጢት መሀል በሆድ ዕቃና በቆለጥ ከረጢት መሀል አስቀድሞ ክፍተት ይኖራል፡፡ ይህ ክፍተት በራሱ የሚገጥም ሲሆን፣ ክፍተቱ ሳይገጥም ከቀረ ግን ቆለጥ ወደ ንፍፊት የሚገባበት፣ አንዳንዴም የሆድ ዕቃ አካላት ሾልከው ወደ ቆለጥ ከረጢት የሚገቡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ያለው የአካል አፈጣጠር ጉድለት በእርስዎ ላይ የታየውን አይነት ችግር፣ በህክምና (testicular torsion) ወይም የቆለጥ መጠማዘዝ የሚያስከትል ሲሆን ሌሎች መዘዞችንም ሊያመጣ ይችላል፡፡
የቆለጥ መጠማዘዝ የቆለጥ ማበጥ፣ ከፍተኛ የህምም ስሜት ምልክቶች የሚያሳይ ሲፓን፣ በፍጥነት ካልታከመ ወደ ቆለጥና አካባቢው ወዳሉ አካላት የሚኖረው የደም ፍሰት በቆለጥ መጠማዘዝ (አብሮ የደም ስሮችም ስለሚጠማዘዙ) ምክንያት ሊስተጓጎል፣ ይህም ቆለትና በአካባቢው ያሉ አካላት ቀስ በቀስ እንዲሞቱ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ችግሩ በእስዎ ላይ እንደሚታየው እያረፈ የሚመጣበት ጊዜ ቢኖርም አንዳንዴ ግን በአንዴ ወደ መጨረሻ የሚባለው ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከፍተኛ የቆለጥ መጠማዘዝ የገጠመው ሰው በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ተገቢውን የቀዶ ጥገና ህክምና ካላገኘ፣ የቆለጥ ህዋሳት ሊሞቱ፣ ይህም ከከፍተኛ የህመም ስቃይ አንስቶ፣ ለመካንነት ሊያጋልጥ ይችላል፡፡
ውድ ዮናስ ፡- ስለ ችግሩ ይህን ካልንዎ ዘንዳ፣ በአፋጣኝ ወደ ከፍተኛ ሐኪም (ከተገኘ ወደ ቀዶ ጥገና ሐኪም) እንዲሄዱ እንመክርዎታለን፡፡ ምንም እንኳ ህመሙ በመሀል እረፍት የሚሰጥዎት ቢሆንም፣ አንዴ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ ግን በቀላሉ የማይመለስ (መመለስ ወደ ማይቻል) ችግር ሊፈጥር ይችላልና መዘናጋት አይኖርብዎትም ልንል እንወዳለን፡፡ ጉዳዩን በዝርዝር ለሐኪምዎ ማስረዳት ከቻሉ፣ ምንም እንኳ ህመሙን ሐኪም ባያየውም፣ መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉና የግድ ህመሙ የሚከሰትበትን ጊዜ መጠበቅ አይኖርብዎትም፡፡ ጤና ይስጥልን!!

No comments:

Post a Comment