Tuesday, December 10, 2013

“የኢትዮጵያ ሕዝብ የአጼ ምኒልክ ዕዳ አለበት” – የ80 ዓመቱ አቶ ከበደ ሙላት


 
minilik በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው እንቁ መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣየ82 ዓመቱ አዛውንት አቶ ከበደ ሙላት ንጋት፤ የተወለዱት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ትምህርታቸውን በሐረር ልዑል ራስ መኮንን ት/ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ በመምህራን ማሠልጠኛ ማዕከል ገብተው የአስተማሪነት ሥልጠና ወስደዋል። በቀድሞው የጽሕፈት ሚኒስቴር መ/ቤት ከ1947 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በባሕር መዝገብ ዳይሬክተርነት፣ በዘውድ ም/ቤት ጸሐፊነትና በሌሎችም ዘርፎች አገልግለዋል። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም አስተደደር ዘመን የኦምዱስማን (የዕንባ ጠባቂ) ተቋም አባል የነበሩት አቶ ከበደ፤ በቀድሞው የሠራተኛ አስተዳደር ኮሚሽን መ/ቤት የአስተዳደር ፍ/ቤት ዳኛም ነበሩ። በ1984 ዓ.ም መጨረሻ በራሳቸው ጥያቄ በጡረታ የተሰናበቱት ዕንግዳችን፤ ባለፉት 22 ዓመታት እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ድረስ ያሉትን አገራዊና መንግሥታዊ መዛግብቶችን በማንበብ፣ በመመርመርና ታሪካዊ መጽሐፍ በማዘጋጀቱ ተግባር ላይ አትኩረዋል። ያዘጋጁት መጽሐፍም ባለ 550 ገጽ ሲሆን፤ የዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥትን የሚመለከት፣ የንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱንና የቀዳማዊ ዐፄ ኃ/ሥላሴን ጊዜያት ዋና ዋና ጉዳዮችን የሚዳስስና የሕትመትን ብርሃን ለማግኘት ስለኢትዮጵያ አንድነት ታሪክና ስለብልጽግናዋ የሚቆረቆሩ ባለሀብት ዜጎችን ድጋፍ የሚጠብቅ ነው። አቶ ከበደን የዳግማዊ ምኒልክን ሥርዓተ ቀብር 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ… ፍቃዱ ማኅተመወርቅ እና ሰሎሞን ለማ አነጋግረዋቸዋል።
kebede ዕንቁ፡- በታሪክ መጽሐፍዎ ረቂቅ ላይ ሦስት ኢትዮጵያን ያስጠሩ መሪዎች ስምና ተግባር መገለጹን ጠቁመውናል። ሦስቱ የሀገራችን መሪዎች እነማን ናቸው? ምኒልክስ ከሦስቱ በምን ይለያሉ?
አቶ ከበደ፡- ሦስቱ ነገሥታት ካሌብ፣ ቴዎድሮስና ዮሐንስ ናቸው። ዐፄ ካሌብ ከሰባ በላይ መርከቦችን ሠርቶና በሠራቸውም መርከቦች ብዙ ሠራዊት ይዞ ወደ አውሮፓ በመጓዝ ድል አድርጎ ስለመመለሱ በታሪክ የተጻፈለት ነው። ዐፄ ቴዎድሮስን ብንወስድ ለኢትዮጵያ ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉና በዓለም ደረጃም እውቅናን ያተረፉ ናቸው። ከደርቡሾች ጋር ሲዋጉ መተማ (ጋላባት) ላይ የወደቁት የዐፄ ዮሐንስ ታሪክ አለ። የዮሐንስ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ክብር ስለሆነም ስመ-ጥሩ ናቸው።
እንግዲህ ከእነዚህ ዐፄ ምኒልክ የሚለዩት፤ ሥልጣኔ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ፣ የውጭ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገራችን እንዲደርስ በማድረጋቸው፣ በጊዜው ታላላቅ ከሚባሉ ከ30 በላይ መንግሥታት ጋር በዕኩልነት ላይ የተመሠረተ ውል መዋዋል በመቻላቸውና በሌሎችም ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ነው። የዲፕሎማሲውን ተግባር በዚህ ሁኔታ ከመጀመራቸውም ባሻገር፤ ምኒልክ አምባሳደሮችንና ቆንስላዎችን ወደየሀገራቱ ልከዋል። የመጡትንም ተቀብለዋል። ለአብነት የቤልጂግ፣ የሩሲያ፣ የኢጣሊያ፣ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ፣ የጀርመን… አምባሳደሮችን ብንወስድ፤ በእሳቸው ጊዜ የመጡ ናቸው። እንደውም ይሄን በመሰለው ተግባር ባበረከቱት አስተዋፅኦ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፈር-ቀዳጅነት ተወዳዳሪ የላቸውም ብዬ እገምታለሁ።
ዕንቁ፡- በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ምኒልክን በማውሳትና አንፀባራቂ ሥራቸውን በማጉላት… ደረጃ ምን የተሠራ ሥራ ነበር?
አቶ ከበደ፡- ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን በሚመለከት ከተሠራው ሥራ አንዱና ዋንኛው፤ በአራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት የሚገኘውና ወደ ዓድዋ መዝመታቸውን የሚገልጸው ሐውልት መቆሙ ነው። ሌላው አስከሬናቸው በክብር ያረፈበት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ስለበጎ ተግባራቸው መታሰቢያ እንዲሆን ተብሎ መታነጹ ነው። እ…
ዕንቁ፡- ግን ያሉት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በስማቸውም ይሁን በብሔራዊ አርአያነታቸው ዘላቂነት ያለው ተግባር በትውልድ ውስጥ መከናወን የሚችልበትን መሠረት መጣልም ይቻል አልነበረም?
አቶ ከበደ፡- ይቻል ነበር በርግጥ… ግን በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ስለዳግማዊ ምኒልክ የተደረገው፤ በየትም ሀገር የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ሁሉ ከሚያደርገው የተለየ አይመስለኝም። ብዙውን ጊዜ መንግሥታት የራሳቸውን ሥራ ያስተዋውቃሉ እንጂ ያለፈውን መንግሥት ታሪክ አጉልቶ የማውጣት ሥራ ሲያከናውኑ ዐይታዩም።
ዕንቁ፡- በዓለም ደረጃ ብንመለከት፤ ሀሉም መጪ መንግሥታት ያለፊውን በጎ ተግባር… የአገራችን ነባራዊም ይሁን ወቅታዊ ታሪክ እንደሚመሰክረው አድበስብሰው ወይም ከነአካቴው እያወገዙም ጭምር ለማዳፈን እንደሚፈልጉት ዓይነት ሥራ አይደለም የሚያከናውኑት። ለምሳሌ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በጃፓን፣ በጀርመን ወዘተ. የሆነውን ነገር ብናጤነው እርስዎ እንደሚሉት አይመስለንም። ከዚህ አንጻር የምኒልክን ወሮታ ማሳነሱ ተገቢ ነው?
አቶ ከበደ፡- ተገቢ አለመሆኑ አያከራክርም። እንደውም አሜሪካን በሄድኩበት አጋጣሚ ያስተዋልኩት ነገር አለ። የቀደሙ መሪዎቻቸውን ሥራዎች ከሚያንጸባርቅ ሁኔታ ጋር… በሐውልት መልክ ቀርጸው ከኋይት ሀውስ ቤ/መንግሥት ፊት ለፊት ሥዕላዊ ገለጻ ባለበት ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ተመልክቼአለሁ። ግን እንደ አሜሪካ የመሰሉትን አገራት ከአፍሪካውያኑ ሀገራት ጋር ማወዳደር አይቻልም።፡ የአፍሪካ መንግሥታት ሁኔታ ትንሽ ለየት ያለ ይመስለኛል። ኢትዮጵያም ያለቸው በአፍሪካ ምሥራቅ ክፍለ ግዛት ነው።
ዕንቁ፡- ምኒልክ ከዐፄ ቴዎድሮስ የተማሩት ብዙ ነው… ስለመባሉ ምን ይላሉ?
አቶ ከበደ፡- ይኼ ትክክል ነው! ዐፄ ቴዎድሮስ ሸዋን ለማስገበር ጦር ጭነው በመጡ ጊዜ ምኒልክ የ12 ዓመት ልጅ ነበሩ። ስለነበሩም የአንኮበር ሰዎች እስከምንጃር ድረስ ይዘዋቸው ሸሹ። በኋላ ዐፄ ቴዎድሮስ አስፈልገው ያዟቸው። ከቤተሰቦቻቸው ጋርም ወደ ጎንደር ወሰዷቸው። ከወሰዷቸው ጊዜ ጀምሮ ግን እንደ ጠላት ወይም እንደ ባላጋራ አልተመለከቷቸውም። ይልቁንም ተንከባክበው በመያዝ ልጃቸውን ወ/ት አልጣሽን ድረው ብርቱ ዘመድ ሊያደርጓቸው ፈልገዋል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ችሎት በሚያስችሉበት ጊዜም ዕውቀቱን እንዲቀስሙ በሚል ከአጠገባቸው ያስቀምጧቸው ነበር።
ዐፄ ቴዎድሮስ በየሄዱበት ምኒልክን ያስከትሉ እንደነበርም ከተጻፈው የታሪክ መዝገብ ላይ አንብቤአለሁ። እንደውም ምኒልክ ደጃዝማች ተብለው በቴዎድሮስ ተሹመዋል። እንደዛ ያከበሯቸው ቢሆንም፣ ሰዎች አጓጉል ምክር መክረዋቸው ነበርና፤ ምኒልክ ከቴዎድሮስ ጋር ተቀያይመው ወደ ግዞት ተላኩ። ለማንኛውም ለዐሥር ዓመት ያህል ምኒልክ ከቴዎድሮስ ጋር ቆይተዋል። በእነዚያ ዓመታትም የመንግሥትን አስተዳደር ዕውቀት ቀስመዋል፤ በኋላ በተፈጥሮአዊ ስጦታቸው ያዳበሩትን የዳኝነት ትምህርትም እንደዚሁ።
ዕንቁ፡- በነበረው አስተሳሰብ መመዘኛ “ምኒልክ የሃይማኖትትና የብሔር መድልኦ የማያደርጉ መሪ ነበሩ…” ስለመባሉ፤ አስተያየትዎ ምንድነው?
አቶ ከበደ፡- ከታሪክ እንደተገነዘብኩት ምኒልክ በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት የሚያወግዙት ወይም የሚጠሉት ሰው አልነበረም። በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን የሰውን ልጅ ዕኩል የሚመለከቱ ንጉሥ ስለመሆናቸው ካነበብኳቸው ታሪካዊ መዛግብቶች ተረድቼአለሁ። ሹመት በሚሰጡበት ጊዜ እንኳ “ይሄ የዚህ ቦታ ሰው ነው፤ የዚያኛው ሥፍራ ተወላጅ ነው…” በሚል አንዱን ከሌላው የማበላለጥ ጠባይ እንደሌላቸው በታሪክ ተመስክሮላቸዋል።
ዕንቁ፡- ምኒልክ የሚነገርላቸውን ያህል ጠላታቸውን መሐሪ ንጉሥ ነበሩ?
አቶ ከበደ፡- ታሪካቸውን ስመረምር የምኒልክ መሐሪነት ተፈጥሮአዊ ጸጋቸው ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሼአለሁ። ይሄንንም የምለው በቂ መረጃ ይዤ ነው። ለምሣሌ በዓድዋ ጦርነት የተማረኩት የጣሊያን ወታደሮች፤ የብቀላ ርምጃ እንዳይወሰድባቸው ጥብቅ መመሪያ ሰጥተዋል። ለምርኮኞች ተስማማሚው ምግብ ጊዜው በፈቀደ መጠን እንዲዘጋጅ አዘው ተግባራዊነቱን አረጋግጠዋል። ከፊሎቹን ምርኮኞች ወደ ቤተ-መንግሥት እንዲቀርቡ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፣ የቀረቡትም ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ብርቱ ጥንቃቄ አድርገዋል።
ከምርኮኞቹ መሀል የምህንድስና ችሎታና ሌላም ሙያ የነበራቸውን በመምረጥ… ኢትዮጵያን በሚጠቅመው ሥራ እንዲሰማሩም ከምርኮኝነት ስሜት የሚመነጭ የመንፈስ ጭንቀት ሰለባ እንዳይሆኑ በብርቱ ጥረዋል። ይሄንንም በማድረጋቸው ለምሣሌ ያህል እነዚያ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ምርኮኞች ቀዳሚውን የአዲስ አበባን ከተማ ማስተር ፕላን አዘጋጅተው ለንጉሡ አስረክበዋል። በነገራችን ላይ እንደ ዕድል ሆኖ ያ ማስተር ፕላን በእጄ ይገኛል። ያዘጋጀሁት ታሪካዊ መጽሐፍ አካልም አድርጌዋለሁ። ሌላው ምንድነው? አንዱ ምርኮኛ ከእናቱ የተጻፈ ደብዳቤ ከጣሊያን ይመጣለታል። ደብዳቤው የወታደሩ እናት መሪር ሐዘኗን የገለጸችበት ነበረ። ምርኮኛውም ደብዳቤውን እንዳገኝ ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን የሰሙት ምኒልክ ያንን ምርኮኛ፣ “አቅርቡልኝ” ይሉና ይቀርባል። ከቀረበም በኋላ ሁኔታውን ተረድተው ሲያበቁ፤ ከምርኮኞቹ ሁሉ ቀድሞ ወደ ሮም እንዲላክ አድርገዋል።…
ዕንቁ፡- ስለውጫሌ ውል የሚነግሩን ይኖራል?
አቶ ከበደ፡- ስለውሉ አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያ በሥፋት ጽፈዋል። ዋናውን ውልም በመጽሐፋቸው ገጽ ውስጥ አካተውታል። እንደሚታወቀው የውሉ ምስጢርነት በኢጣሊያ ቋንቋ የተጻፈውና የአማርኛው ትርጓሜ የተለያየ መሆኑ ነው። በስተኋላ ግን ያ አነጋጋሪ… ውል፤ ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ጥይት… ተደብድቦ ወድቋል። በርግጥ የውጫሌን ውል ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የኢጣሊያ መንግሥት ራሱ “ከዛሬ ጀምሮ… ውድቅ ሆኗል” ብሎ በመሪው በኩል ለኢትዮጵያ መንግሥት የጻፈው ደብዳቤም አለ። ይኼም በእኔም ይሁን በተክለጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ነው።
ዕንቁ፡- ከዳግማዊ ምኒልክ ብሔራዊ አብነቶች ጥቂቱን ቢገልጹልን?
አቶ ከበደ፡- የምኒልክን ብሔራዊ አብነት፤ የባሪያ ንግድን ለማሰቆም ከወሰዱት ብርቱ አቋም ጀምረን እንደተባለው በጥቂቱ መግለጽ ይቻላል። በዘመነ-መንግሥታቸው መጀመሪያ ሰሞን ሰዎች “ባሪያ” እየተባሉ እንደሸቀጥ ይሸጡ፣ ይለውጡ ነበር። በዚህ በኩል የነበረውን ነውረኛ ተግባር ለማስቆም ቴዎድሮስ የወሰዱት ጅምር ርምጃ ነበር። ምኒልክ ከዛ ተነስተውና በራሳቸውም ሐሳብ ተመርተው፤ ባሪያዎችን ነጻ የሚያወጣ ዐዋጅ ከአንድም ሁለት ጊዜ አውጀዋል። የፀረ-ባሪያ ንግድ ዐዋጃቸውን በማድነቅም፤ ንግሥት ቪክቶሪያ የምሥጋና ደብዳቤ ልከውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆቹን እንዲያስተምር፣ አላስተምርም ካለ ደግሞ በንብረቱ እንዲቀጣ የሚደነግገውን ዐዋጅም፤ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ያወጡ፣ ያለ ጎሳ፣ ያለ ሃይማኖት እና ያለ ጾታ… ልዩነት፤ መኳንንቶቹን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ከሰባት ዓመት ዕድሜአቸው ጀምሮ ወደ ት/ቤቶች እንዲልኩ፤ የማይልኩም ከሆነ በንብረታቸው የሚቀጡበትን መመሪያ ያመነጩ፣ ተማሪዎች ከትምህርት ማዕድ እንዳይሸሹም፤ የኪስ ገንዘብ እየተከፈላቸው የሚማሩበትን ሁኔታ ያመቻቹ፣ ግዑዛን ታሪካዊ ቅርሶች እንደሚያረጋግጡትም፤ በስማቸው የሚጠሩትን የዘመናዊ ዕውቀት መቅሰሚያ ማእከሎች የመሠረቱ ንጉሥ ምኒልክ ናቸው። ለምሣሌ ደጃዝማች ተፈሪ (ኃ/ሥላሴ) ከሐረር መጥተው በአቋቋሙት ት/ቤት እንዲማሩ ያደረጉም እሳቸው ናቸው። እሳቸው አዲሲቷ ኢትዮጵያ በወጣት ልጆቿ አንድትከበር፣ የልማቷም ጅምር ዳር መድረስ የሚችልበትን ጽኑ መሠረት እንዲይዝ የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል።
ሌላው የዐፄ ምኒልክ ብሔራዊ አብነት የምለው፤ ሃይማኖትን በተመለከተ ያከናወኑትን ተግባር ነው። በቀድሞ ጊዜ “ኢትዮጵያ የክርስቲያኖች ሀገር ናት…” ያሰኘውንና ለዚህም እንደመነሻ የሆነውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እንዲከበር፤ ቤ/ክርስቲያናትን በማሠራትና የፈራረሱትን እንዲጠገኑ በማድረግ ረገድ… የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ነው። እንደዚሁም ከጎረቤት መንግሥታት ጋር በመስማማት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለይተው ማኖራቸው፣ በሦስት አዋሳኝ ቦታዎችም የድንበር ማካለያ ምልክቶች እዲቀመጡ ማድረጋቸውና ወደ ጎረቤት ሀገራት ተካለው የነበሩትን ወይም የተወሰዱትን የኢትዮጵያ ይዞታዎች ያስመለሱ መሆኑ ዋንኛው ብሔራዊ አብነት ነው።…
ዕንቁ፡- ለምሣሌ የትኞቹን ይዞታዎች ነው ያስመለሱት?
አቶ ከበደ፡- በሱዳን፣ በሶማሌያና በሌሎችም የጎረቤት ግዛቶች ተካተው የነበሩ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ይዞታዎች እንዲመለሱ አድርገዋል። ከየአጎራባች ሀገራቱ የተመለሱት የኢትዮጵያ ይዞታዎች “እነዚህና እነዚያኞቹ… ናቸው…” ማለቱን ግን ለጊዜው ትቼዋለሁ።
ዕንቁ፡- ለምን፣ አቶ ከበደ?… ጊዜ ማለት እኮ እንደ እርስዎ በዕድሜ አንጋፋ የሆነ ኢትዮጵያዊ በሚመሰክረው ቃል እውነቱ የሚንጻባረቅበት ይሄን የመሰለው በጎ አጋጣሚም ይመስለናል… ተሳስተን ይሆን?…
አቶ ከበደ፡- አልተሳሳታችሁም። ነገር ግን እንዳላችሁትም ብቻ አይደለም። ጊዜ ማለት ሌላም ነገር ነው። “ከሱዳን አገር የትኛውን?” ሲባል… ይኼኛውን ብል፤ ችግር ይፈጥራል። “ከሶማሌስ የትኛውን?” ሲባል… ያኛውን በማለት ብመልስ እንደዛው ነው። ስለዚህ ጊዜው እስኪፈቅድ ለጊዜው መተዉ ይሻላል። ይልቅስ በአንድ ወቅት አሁን በተቃዋሚ መድረክ ውስጥ የሚገኙት ደ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዝዳንት ሆነው እያለ የተናገሩትን አስታውሳዋለሁ። ዶ/ር ነጋሶ በቤተ-መንግሥት በነበሩበት ጊዜ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ወደ ውጭ ተካለው የነበሩትን የኢትዮጵያን መሬቶች የማስመለሱን ጉዳይ እንደጥፋት ወይም እንደነውር ቆጥረው ሲናገሩ የሰማሁ ይመስለኛል። ይህን መሰሉም ሁኔታ በጣም ይደንቀኛል። ኢትዮጵያ እንድትሠፋ እንጂ እንድትጠብ የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ሊኖርም አይችልም። እና ያ ትዝብት እስከ አሁን በአዕምሮዬ ውስጥ አለ። ለማንኛውም ምኒልክ ኢትዮጵያን ለማስፋት፣ ወደ ቀደመ ይዞታዋ ለመመለስ ጥረት ካደረጉ ነገሥታት አንዱና ዋንኛው ናቸው።
ዕንቁ፡- ዛሬ “አነስተኛና ጥቃቅን…” በሚባለው መስክ ለተደራጁት የቀድሞዎቹ “አንጥረኞች፣ አቀርባዮች፣ ባለእጆች…” ቀዳሚውን ብሔራዊ ዕውቅና የሰጡትና ሕዝቡ ባለሙያዎቹን እንዳይንቅ መመሪያ… ያስተላለፉት ምኒልክ አይደሉምን?
አቶ ከበደ፡- ትክክል ነው…! “ሸማኔ፣ ብረት ቀጥቃጭ፣ ሌላውም የእጅ ሥራ የሚሠራው ባለሙያ ሁሉ፤ ለሀገሩ የሚጠቅም ነውና መሰደብ፣ መነወር የለበትም…” በማለት በአደባባይ ያስተማሩ ንጉሥ ምኒልክ ናቸው። ለምሣሌ ሸማኔነት… (የጥበብ ባለሙያ ሆኖ መገኘት…) ያሰድብ ነበር። ያንን የመሰለ መጥፎ ልማድ ከሕዝቡ ለማስጣልና ባለሙያው በሙሉ እንዲከበር፣ በሥራው እንዲበረታታ ለማድረግ ዐዋጅ ያወጡ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በፍጹም የሚካድ አይሆንም።
ዕንቁ፡- ምኒልክ ከፍ ብለው የገለጹትንና ሌሎችንም ብሔራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አብነቶች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን አብርክተው ሳለ፤ እንደሠለጠነው ዓለም በተከታታይ ትውልድ ውስጥ የሚገባቸውን የባለውለታነት ዋጋ ባለማግኘታቸው ምን ይሰማዎታል?
አቶ ከበደ፡- እኔ ሰው በሠራው ሥራ በሕይወት እያለም ይሁን ከሞተም በኋላ መከበር አለበት፤ ታሪኩም መጻፍ፣ መነገር፣ ለትውልድ ማስተማሪያ፣ መኩሪያ መሆኑ መገለጽ ይኖርበታል የሚል እምነት ስላለኝ፤ የምኒልክ ውለታ ተገቢውን ዋጋ ሊያገኝ ባለመቻሉ በእጅጉ አዝናለሁ።…
ዕንቁ፡- እንደ ታሪካዊ መጽሐፎች ምስክርነት፤ ምኒልክ ስመ-ጥሩ መሆናቸው… የሚያከራክር አይደለም። ግን ደካማ ጎን አልነበራቸውም ማለት ይቻላል?
አቶ ከበደ፡- በቅድሚያ ምኒልክ መገምገም ያለባቸው፤ በሥራ ዘመናቸው ባከናወኑት ተግባር ብቻ መሆን አለበት። ዛሬ ያለነው 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ነው። ምኒልክ የነበሩት በ19ኛው ክ/ዘመን ነው። ስለዚህ መመስገንም ይሁን መወቀስ ካለባቸው በዚያን ዘመን በሠሩት ሥራ ብቻ ነው። በዛ ዘመን ስለሠሩት ሥራ፤ እኔ የጻፈኩትን ጨምሮ የጳውሎስ ኞኞንም ይሁን የሌሎቹን ታሪካዊ መጸሐፎች በእውነት ጊዜ አግኝቶ ላነበበ ሰው፤ ንጉሡ የሠሩትን ሥራ ቁልጭ ብሎ ያገኘዋል። ለምሣሌ ጳውሎስ ኞኞ የደርግ ባለሥልጣኖች ፈቅደውለት ባዘጋጀው ታሪካዊ መጽሐፍ፤ ስለምኒለክ ያገኘውን መረጃ ሙሉ በሙሉ አለመውሰዱ ይታያል። በእኔ አስተያየት እሱ በጣም የተወሰነውን መረጃ ነው ለመጽሐፉ ግብዓት ያደረገው። ይህን የምለው የጳውሎስን በጎ ተግባር ለማናናቅ ሳይሆን፤ ምኒልክን በተመለከተ እሱ በመጽሐፉ ውስጥ ካካተተው የሚበልጥና የሚያስደንቅ ማስረጃ ያለ መሆኑን ለመጠቆም ፈልጌ ነው።
እና የሰው ልጅ ጥሩ ሥራ በሠራ ቁጥር፤ በውስጡ ድክምቶች ሊያኖሩበት አይችሉም የሚለው መደምደሚያ ላይ መድረስ አይቻልም። ስንዴ የዘራ ሰው የሚያመርተው ስንዴ ብቻ አይደለም። አረምም በውስጡ አለ። የሰው ልጅ ሁሉ እንደዚህ ነው።
ዕንቁ፡- “የምኒልክ መስፋፋት ያስከተለው ቁርሾ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር ሆኗል። ለምሣሌ ከነባሩ ባለይዞታ መሬት እየነጠቁ ለነፍጠኞችና ለአዝማቾቻቸው ማደላቸውና ይኸውም በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ሥር ሰዶ እንዲቀጥል ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው የሚገለጽ ነው። ይህም ሁኔታ ብዙኃኑን ኢትዮጵያዊ ለገባርነት አጋልጦታል…” ስለሚባለው አስታራቂ ሐሳብ ይኖርዎታል?
አቶ ከበደ፡- የሚባለው በወሬ ደረጃ የሚታሰብ ነው ብዬ እገምታለሁ። በመሠረቱ ምኒልክ ርስት መትከላቸውን የሚገልጽ እንጂ ርስት ስለመንቀላቸው የሚያትት ታሪክ አላነበብኩም። ምናልባት አሁን ባለው የለውጥ ሒደት፤ አንዳንድ ቅር የተሰኙ ወገኖች እንደሚባለው ሊሉ ይችላሉ። እንዲህ የሚሉት ግን በማስረጃ ተደግፈው ሳይሆን በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመሥርተው እንደሆነ ነው የምገነዘበው።
ዕንቁ፡- አይደለም… አባባሉ፣ “በመረጃም የተደገፈ ጉዳይ ነው…” ብለው የሚሟገቱ ወገኖች አሉ። ለምሣሌ፣ “ምኒልክ በጣሉት መሠረት ላይ ተንደርድረው በዐፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን የመጡት እንደ ራስ መስፍን ስለሺ ያሉት ሰዎች፣ “ይሄ መሬት ምን ይበቃኛል? ምንስ ያጠግበኛል?…” እያሉ የብዙ ጋሻ መሬት ባለቤት የሆኑት፤ የአያሌ ዜጎችን ርስት እየነቀሉ እንደነበርስ ማስተባበል ይቻላል?
አቶ ከበደ፡- አስቀድሜ ተናግሬአለሁ፤ ሁሉም በዘመኑ በሠራው ሥራ ይመዘናል። እንዴ? ምኒልክ እኮ በጊዜያቸው የነበረ አንድ ባላባት፣ “ንጉሥ ሆይ! እባክዎ ርስቴን ይወረሱ…” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ፣ “ኢትዮጵያ የማን ሆና ነው የአንተን የግል ርስት የምወርሰው?” በማለት መልስ የሰጡ ናቸው። ሌላ ሌላውን እንተወውና፤ ምኒልክ እኮ የግል ርስት አልነበራቸውም። “ታላቁ ቤተ-መንግሥት” ብለን ከምንጠራውና ከሚኖሩበት ቤት በቀር ያለፈ የግል ሀብትም ይሁን ጥሬ ገንዘብ፣ ርስተ-ጉልት… እንዳልነበራቸው፤ በታሪክ ማስረጃ የተረጋገጠ ነው። በበኩሌ በእሳቸው ዘመነ-መንግሥት ርስትን ከአንዱ ኢትዮጵያዊ ነቅሎ ለሌላው ኢትዮጵያዊ መስጠት ወይም ከነአካቴው ርስት አልባ የማድረግን ርምጃ የሚገልጽ ታሪካዊ ሠነድ እስከ አሁን አላነበብኩም። በርግጥ አሁን የጎሳ አስተዳደር ከተፈጠረ ወዲህ፤ በነበረው የምኒልክ አስተዳደር አልስማማም የሚለው ወገን ወይም ክፍል በኩል፤ በዋናውም ይሁን ማብራሪያን የሚሻ በሚመስለው ተከታይ ጥያቄ ውስጥ የተንጸባረቀውን የሚመስል ሐሳብ ሲነገር እሰማለሁ። ነገር ግን ትክክል ነው ብዬ አልቀበለውም።
ዕንቁ፡- ኤርትራንም ይሁን የባሕር በር ስላሳጠን፣ የፓለቲካ እሳት ማስነሻና ማግለብለቢያ እየሆነም ከዘመን ዘመን በመሻገር ላይ ስለሚገኘው የመረብ ምላሽ ጉዳይ በተመለከተ፤ ዳግማዊ ምኒልክ በታሪክ ተወቃሽና ተከሳሽ ሆነው ስለሚቀርቡበት ሁኔታስ ምን ይላሉ?
አቶ ከበደ፡- ደህና… “የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት እንደተጠናቀቀ ምኒልክ ለምን ከመረብ ማዶ ወዳለው የኢትዮጵያ ግዛት ገፍተው ሳይሄዱ ቀሩ?” እየተባለ መነገሩ አዲስ ነገር አይደለም። በጊዜው የምኒለክ ጦር እንጢቾ የተባለው ሥፍራ ድረስ ሄዷል። እሳቸውም በሥፍራው ተገኝተዋል። ሰሚ ጠፋ እንጂ ከዚያ እንዲመለሱ ያደረጓቸው በቂ ምክንያቶች ነበሩ። ከምክንያቶቹም አንደኛው፤ አስቀድመው ያቀኑት የኢትዮጵያ ክፍለ-ግዛት ሕዝብ ወደቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እንቅስቃሴ ማድረጉን መስማታቸውና ዜናውን እንደሰሙም፣ “የካብኩት እንዳይናድ ብመለስ ይሻላል” ወደሚለው ውሳኔ ማዘንበላቸው ነው።
ሁለተኛው ምክንያት ሰራዊታቸው ይዞት የዘመተው መጠነኛ ስንቅ ያለቀበት መሆኑ ነው። ደግሞም በጦርነቱ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ ጽኑ ረሀብ መከሰቱም ይሁን ከፍተኛ የሆነ የከብት ዕልቂት የመከሰቱም ሁኔታ ተደማሪ ምክንያት ነበረ። ይኼም ብቻ ሳይሆን፤ በተካሄደው ፍልሚያ የተዋጊው ኃይል ቀንሷል።
ሌላውና ዐብይ የሆነው ምክንያት፤ የኢጣሊያ መንግሥት የላከው አዲስ የጦር ኃይል ምፅዋ የደረሰ መሆኑ ነው። እንግዲህ በሕመምና በምግብ እጥረት የተዳከመውንና አስቀድሞ በተካሄደው ውጊያ የሰው ኃይሉ የተመናመነውን ሠራዊት ይዘው ከመረብ ማዶ ቢሻገሩ፤ ምን ነበር ሊሆን የሚችለው? ብሎ ነገሮችን ማጤን ተገቢ ይመስለኛል። ምናልባት ምኒልክ በተገለጸው ሁኔታ ላይ ሆነው ወደፊት ቢቀጥሉ፤ ጨብጠውት የነበረውን ድል የማጣት መጥፎ ዕድል አይገጥማቸውም ማለት አይቻልም። ስለዚህ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገብተው ወደዛሬይቱ ኤርትራ መሬት ገፍተው ሳይሄዱ ቀርተዋል እንጂ፤ ምኒልክ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ግዛት ተገንጥላ እንድትቀር ሙሉ ፍላጎት ኖሯቸው እንዳልነበር ተረድቼአለሁ።
ዕንቁ፡- በምኒልክ የተነሣሣው ሥልጣኔን የመከተል ሁኔታ፤ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን መሥመር ይዞ ወደ ደርግም የቀጠለበትን ሁኔታ መመልከት ተችሏል?
አቶ ከበደ፡- ሁሉንም ነገር ማሥመር የሚያስችለው የጊዜና የእውቅት መጣመር ነው። በእውቀት ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል። በምኒልክ ዘመነ-መንግሥት ትምህርት ተጀመረ እንጂ ብዙ የተማሩ ሰዎችን ማፍራት ተችሎ በእነዚያ ስዎች የመጠቀም ዕድል አልተገኘም። በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ት/ቤት ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የተስፋፋ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ማለት የምኒልክ ጅምር ሒደት በዘርፉ ቀጥሏል። እንደውም በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመኑ-መንግሥት በሀገር ውስጥም ይሁን ወደ ውጭ ተልከው የተማሩት ወጣቶች፤ የዴሞክራሲን ጣዕም እየቀመሱ መጥተው ያንን ጣዕም ተግባራዊ ለማድረግ ባደረጉት ሙከራ መንግሥታዊ ለውጥ መጥቷል። ያ መንግሥታዊ ለውጥም ክፉ ነው ማለት አይቻልም። ለምሣሌ የደርግን መንግሥት ብንወስድ፣ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅድም” ነበር ያለው። ግን… ደሙ ቀደመ። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ አሁንም፣ ምንጊዜም ቢሆን ለሕዝብ አክብሮት የሚሰጥ፤ የሕዝብን ምክር፣ የበላይነት የሚቀበል መንግሥት ማግኘት አለባት።
ዕንቁ፡- የዳግማዊ ምኒልክ ሥርዓተ-ቀብር የተከናወነበት 100ኛ ዓመት በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩ… ያሳደረብዎ ቁጭት አለ?
አቶ ከበደ፡- በእውነቱ መቶኛ ዓመቱ በብሔራዊ ደረጃ መከበር ያለበት መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ የዐፄ ምኒልክ ዕዳ አለበት። ዕዳውንም መክፈል አግባብ ነው። ከዚህ አንፃር ስመለከተው በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩ በጣም ያሳዝናል። ለምሣሌ ዮዲት ያን ሁሉ ጥፋት አጥፍታ፣ ግራኝ መሐመድ ያን ሁሉ ጥፋት አጥፍቶ፤ በታሪክ ውስጥ ግን ስማቸው አለ። ምኒልክ እጅግ ብዙ ሥራ ለኢትዮጵያ አበርክተው፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚወዱና ስለዚህም መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁ ሰው ሆነው ሳለ፤ የእሳቸው ጉዳይ ቀለል ተደርጎ መታየቱ… ከታሪክ ጋር እንዳያጣለን እፈራለሁ። ወጣቱም ትውልድ ቢሆን ይሄን የመሰለውን ሁኔታ የሚደግፍ አይመስለኝም።
ዕንቁ፡- ምኒልክ የሞቱበት ትክክለኛ ጊዜ ይታወቃል?
አቶ ከበደ፡- የምኒልክ ሞት ለብዙ ጊዜ ተደብቆ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። የዚህም ምክንያት እሳቸውን “እተካለሁ” የሚለው የመንግሥታቸው ካቢኔ ሞታቸው እንዳይታወቅ ከመፈለጉ ጋር የተያያዘ ከመሆን አያልፍም። ምናልባትም እንደዚያ የተደረገው ጸጥታው እንዳይበላሽ በመስጋት ይመስለኛል። መርዶው በወቅቱ ሳይነገር ተደብቆ የቆየውም ለሦስት ዓመት ጊዜ ያህል መሆኑ በሥፋት የሚነገር ነው። እንዲያም ሆኖ ግን በምስጢር ለምኒልክ ተዝካር ያወጡ አንዳንድ መኳንንቶች እንደነበሩ የጽሑፍ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። ያም ቢሆን እስከ ዛሬም ድረስ በጽሑፍ የሰፈረና ስለአሟሟታቸው አንዴትነትና ስለሞቱበት ጊዜ የሚገልጽ መረጃ ላገኝ አልቻልኩም። በዚህ በኩል ያለው ክፍተት እኔንም ሆነ ሌሎችን ለጥናትና ለምርምር የሚጋብዝ ነው።
ዕንቁ፡- አቶ ከበደ፣ ከእኛ ጋር ስላደረጉት ቆይታ በመጽሔታችን አንባቢዎች ስም እናመሰግኖታለን!
አቶ ከበደ፡- እግዚአብሔር ያክብራችሁ!

ምንጭ፣ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/10682

No comments:

Post a Comment